ከ63 ዓመታት በፊት በአውስትራሊያዊቷ ፋና ወጊ የቀዶ ጥገና ሐኪም ዶክተር ካትሪን ሃምሊን እና ባለቤቷ ዶ/ር ሬግ ሃምሊን የተመሠረተው ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ እጅግ አሰቃቂ የሆነው የወሊድ ጉዳት ወይም የማሕፀን ፊስቱላ የደረሰባቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለማከም ቁርጠኛ አቋም አለው።
ዛሬ ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የሃምሊን አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል፣ አምስት ክልላዊ ሃምሊን የፊስቱላ ሆስፒታሎች፣ ሃምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ፣ ከ90 በላይ በሃምሊን የሚደገፉ አዋላጅ ክሊኒኮች እና የሃምሊን ማገገሚያ እና መልሶ ማቋቋም ማዕከልን (ደስታ መንደር) ያካትታል።
ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የማሕፀን ፊስቱላን በዓለም ዙሪያ ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ዋቢ ድርጅት እና መሪ ሆኖ ሴቶችን ሰብአዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ፣ ጤናቸውን እና ደኅንነታቸውን እንዲያስጠብቁ እና በቤተሰባቸው እና ማኅበረሰባቸው ውስጥ የነበራቸውን ሚና መልሰው እንዲያገኙ የሚያስችል ሁለንተናዊ የሕክምና እና እንክብካቤ መንገድ በመፍጠር ፋና ወጊ ነው።
የማሕፀንፊስቱላአሳዛኝሁኔታእናየሃምሊንተስፋ
በሴቶች ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ አስከፊ ነገሮች መካከል አንዱ የማሕፀን ፊስቱላ ወይም በምጥ መስተጓጎል ምክንያት የሚደርስ የውስጥ ጉዳት ሲሆን ሴቷ እራሷን እንዳትቆጣጠር ብሎም በማኅበረሰቧ የተገለለች እንድትሆን የሚያደርግ ነው።
የሃምሊን ቡድን የትኛዋም ሴት በማሕፀን ፊስቱላ ክብሯ መጎዳት እንደሌለባት ያምናል። የዶክተር ካትሪን ሃምሊን ሕልም ፊስቱላን ለዘላለም ማጥፋት ነበር – እና በእርስዎ ድጋፍ ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ እየተቃረብን ነው።
ከፊስቱላ ስቃይ ወደ ብሩህ ተስፋ የሚለውን የውባንቺን ታሪክ ከታች ይመልከቱ።
ሦስቱ ፕሮግራሞቻችን
የሕክምና ፕሮግራም
ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከአሰቃቂ እና መከላከል ከሚቻል የወሊድ ጉዳት ወይም የማሕፀን ፊስቱላ የተረፉ ሴቶችን ጤና እና ክብር ለማረጋገጥ የቆመ ነው።
ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፊስቱላ ሕክምና ቴክኒኩ የታወቀ ነው። በዶክተር ካትሪን ሃምሊን የተገነባው ይህ ፈር ቀዳጅ የቀዶ ጥገና ዘዴ በዓለም ጤና ውስጥ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ዕውቅና አግኝቷል።
አብዛኛውን ጊዜ ፊስቱላ በአንድ ሕይወትን በሚቀይር ቀዶ ጥገና ሊድን ይችላል። ይህም ለአንዳንዶች ከሁለት ሰዓት ያልበለጠ ጊዜ ብቻ ሊወስድ ይችላል።
የማገገሚያ እና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም
ሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ባለፉት 63 አመታት ከ70,000 በላይ የሚሆኑ ለማሕፀን ፊስቱላ የተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ጤና እና ክብር መልሷል። ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን የፊስቱላ ታካሚን ማከም በፊኛ ላይ ያለውን ቀዳዳ ማከም ብቻ ሳይሆን ሴትን በሙሉ በፍቅር እና በጥንቃቄ ማከም እንደሆነ ሁልጊዜ ያምኑ ነበር።
ለዚህም ነው በሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከፊስቱላ ጉዳት የሚያገግሙ ሴቶችን የበለጠ ለመደገፍ የማገገሚያ እና የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ያዘጋጁት። ፕሮግራሙ የሃምሊን የሕክምና ሞዴል ያቀፈ እና ሴቶች በነጻነት እና በክብር ሕይወታቸውን እንዲመሩ የሚያስችል ነው።
የመከላከል ፐሮግራም
የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የማሕፀን ፊስቱላን ለማጥፋት ያለውን ራዕይ ለማሳካት በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ተጨማሪ አዋላጆች ያስፈልጉናል። አዋላጆች የእርግዝና ችግሮችን በመለየት የፊስቱላ ጉዳቶችን አስቀድመው መከላከል ይችላሉ።
ለዚህም ነው እ.አ.አ. በ2007 ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን በመላው ኢትዮጵያ ለማሳደግ የሃምሊን አዋላጆች ኮሌጅን ያቋቋሙት። የሃምሊን አዋላጆች ኮሌጅ በኢትዮጵያ የአዋላጆች ሥልጠና የልህቀት ማዕከል ነው።
የክሊኒካል እና የፕሮግራም ቡድናችንን ያግኙ
የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ቡድን 100% በኢትዮጵያዊያን የተዋቀረ ሲሆን ወደ 600 የሚጠጉ ባለሙያዎች አሉት። ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ በዶክተር ካትሪን ሃምሊን የሠለጠኑ ሲሆን በሃምሊን የሕክምና ሞዴል በማሕፀን ፊስቱላ የተጎዱ ሴቶችን ለማከም በድርጅቱ ውስጥ ይሰራሉ፤ የካትሪንን እና የሬግን ራዕይ እና ስራንም አስቀጥለዋል። የእኛን የሕክምና፣ የማገገሚ እና የመልሶ ማቋቋም፣ እንዲሁም የመከላከል ቡድን አባላትን ለማግኘት ከዚህ በታች ጠቅ ያድርጉ።