የማሕፀን መውጣት (ኦርጋን ፕሮላፕስ) ምንድን ነው?

«የታካሚዎቼ ክብር ሲመለስ በፊታቸው ላይ የሚነበበው ፈገግታ የሥራዬ ምርጥ ክፍል ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን እናቶች ደኅንነታቸው ተጠብቆ የእርግዝና የወሊድ እና ከልጆቻቸው ጋር ደስተኛ የሆነ ሕይወትን እስኪያገኙ ድረስ ሥራዬን አላቆምም።»

ዶ/ር ለታ የሕክምና ዳይሬክተር እና የቀዶ ሕክምና ሐኪም፣ የሐረር የሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል

የማሕፀን መውጣት (ኦርጋን ፕሮላፕስ) ምንድን ነው?


ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከፊስቱላ ሕክምና በተጨማሪ የማሕፀን ችግሮችን የሚያክም ሲሆን ይህም ሕክምና የማሕፀን መውጣት በሽታን ያካትታል። ማሕፀን ከመደበኛ ቦታው ሲወጣ እና እብጠትን ሲፈጥር የሴቶችን ጤና በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል። ይህ ጉዳት በአብዛኛው የብልት እብጠትን የሚያስከትል ሲሆን በወቅቱ ሕክምና ካላገኘ እየተባባሰ መጥቶ የኩላሊትን ሥራ በማደናቀፍ ወደ ኢንፌክሽን ሊያመራ ይችላል። ስለዚህ እንደፊስቱላ ሁሉ የማሕፀን መውጣት ችግርም በተመሳሳይ መልኩ በሴቶች ላይ አስከፊ የሆነ አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ተፅእኖዎ ሊያስከትል ይችላል።

ይህ ሕመም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተግዳሮት


የማሕፀን መውጣት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶችን በተለያየ ደረጃ ያጠቃ ሲሆን በአፍሪካ ይህ ሕመም ያለባቸው ሴቶች በአብዛኛው የሕክምና ተደራሽ ሲሆኑ አይታዩም። በኢትዮጵያ ያለው ከፍተኛ የሆነ የወሊድ መጠን፣ ያለ ዕድሜ ማርገዝ፣ በሕፃንነት ጊዜ የነበረ የምግብ እጥረት፣ ለጤና አጠባበቅ ዕድል የሚሰጠው ውሱን ዕድል እና ከልክ ያለፈ የጉልበት ሥራ ጫና በአብዛኛው ለማሕፀን መውጣት ችግር የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው። ብዙ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ በሚከሰት የማሕፀን መውጣት በሽታ አብዛኛውን ጊዜ እንደ ደም መፍሰስ እና ከባድ ኢንፌክሽ ያሉ ችግሮችን ያስከትላል።

የማሕፀን መውጣት ሕመምተኞች ተስፋ


ለማሕፀን መውጣት በሽታ ለተጋለጡ ሴቶች የሚደረግ ሕክምና የሴቶችን ጤና እና የሕይወት ጥራትን በእጅጉ ሊያሻሽል ይችላል። በኢትዮጵያ ለእናቶች ጤና ትኩረት የሚሰጥ ቢሆንም የማኅበራዊ ጤና ችግር ለሆነው በማሕፀን መውጣት በሽታ ለተጋለጡ ሴቶች ግን በቂ ትኩረት አልተሰጠም። እንደ ዕድል ሆኖ፣ የሃምሊን ሆስፒታሎች ለከፍተኛ ደረጃ የማሕፀን መውጣት ችግር የቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎች ያሏቸው ሲሆን ይህ ወሳኝ ሕክምና ያለክፍያ በነጻ ይሰጣል።

የእማማ ታሪክ


እማማ ዕድሜያቸው 60 ሲሆን በቅርቡ ለ10 ዓመታት ሲሰቃዩበት የቆየውን የማሕፀን መውጣት ሕመም በባሕር ዳር ሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል የተሳካ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው ድነዋል።

እንደሳቸው አገላለጽ፦ «ምን እንደተፈጠረብኝ ለማንም ሰው መንገር አሳፍሮኝ ነበር፤ ችግሩን ለባለቤቴ እንኳን አልነገርኩትም ነበር። ከባለቤቴ ጋር አልጋ ለይቼ ለመኖር ብሞክርም ይህ ችግር ላለፉት 10 ዓመታት የዕለት ተዕለት ጭንቀቴ ከመሆን አላረፈም ነበር።»

እማማ በሃምሊን በነጻ ባገኙት ቀዶ ሕክምና በመጠቀም ሕይወታቸው እንደተለወጠ ገልጸዋል። «ስለፈወሳችሁኝ እና በቀሪው ሕይወቴ ደስተኛ ሆኜ እንድኖር ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ» በማለት ገልጸዋል።