በወሊድ ጊዜ የሚፈጠር ፊስቱላ ምንድነው?

«እነዚህ ሴቶች ያዩት መከራ ማንኛዋም ሴት መሸከም ከምትችለው በላይ ነው። አንዳቸውን እንኳ ማወቅ ማለት ውስጣችሁን የሚነካ እና በልባችሁ ያለውን በጣም ጥልቅ ርህራሄ ፈንቅሎ የሚያወጣ ተሞክሮ ነው።» 

ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን

በወሊድ ጊዜየሚፈጠር ፊስቱላ ምንድነው


አንዲት ሴት ሊያጋጥሟት ከሚችሉት እጅግ ከባድ ነገሮች አንዱ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ ነው። በወሊድ ወቀት የምጥ ሂደቱ እንቅፋት ሲገጥመው በሚፈጠር ውስጣዊ ጉዳት በፅንሱ መተላለፊያ/በርዝ ካናል/ እና በሽንት ፊኛ መካከል ወይም በፅንስ መተላለፊያ እና ፊንጢጣ መካከል ሽንቁር ሲፈጠር ፊስቱላ ይባላል። በዚህ ወቅት ሽንት ወይም ዓይነ ምድር፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሁለቱንም መቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተው ሊያመልጣቸው ይችላል።

በሚያሳዝን ሁኔታ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ ከያዛቸው ሴቶች መካከል 93 በመቶዎቹ የሚወልዱት ሕይወቱ ያለፈ ሕፃን ነው። ይህም አብዛኛውን ጊዜ በጣም ረዥም እና ስቃይ የተሞላበት ለቀናት የሚቆይ ምጥን ተከትሎ የሚመጣ ነው። በተጨማሪም ጥራት ያለው የሕክምና ክትትል ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት በየዓመቱ 1000 ሴቶች አዲስ የፊስቱላ ጉዳት ያጋጥማቸዋል። ይህ አስከፊ ጉዳት ሴቶችን በስቃይ፣ ኀፍረት እና መገለል ወደ ተሞላ ሕይወት ይመራቸዋል።

ምንም እንኳን ይህ ሁኔታ ፍጹም እንዳይከሰት ማድረግ ቢቻልም፤ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ያሉ ሰዎች ላይ አሁንም የተጋረጠ የማኅበረሰብ ጤና እክል ነው። እኛ በኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል የምንገኝ ሰዎች እያንዳንዷ ሴት ያለጉዳት ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ልጅ መውለድ እንድትችል መደረግ እንዳለበት እናምናለን።

በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ እንዴት ይከሰታል?


በዓለም ላይ ወደ 5 በመቶ የሚጠጉ ነፍሰጡር ሴቶች የምጥ ሂደት መስተጓጎል ይገጥማቸዋል። አስቸኳይ የወሊድ ወቅት ሕክምና የማይገኝ ከሆነ ደግሞ፤ መፍትሔ ያልተገኘለት የምጥ ሂደት መስተጓጎል በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ መንሥዔ ሊሆን ይችላል። በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ ዋንኛ መንሥዔ፤ ወቅታዊ እና ጥራቱን የጠበቀ የእናቶች ጤና እንክብካቤ ተደራሽ አለመሆን ነው።

የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡-

  • አንዲት ሴት በወሊድ ወቅት የምጥ ሂደቷ ቢስተጓጎል ምርመራ እና ክትትል በማድረግ ተገቢውን የሕክምና መፍትሔ ማመልከት የሚችሉ ክኅሎት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት ሊኖር ይችላል።
  • አንዲት ሴት አስቸኳይ የሕክምና ክትትል በሚያስፈልጋት ወቅት የሕክምና ተቋማት፣ የብቃት እና የአቅርቦት እጥረት ሊኖር ይችላል።
  • አንዲት ሴት ወደ ጤና ማእከል መሄድ እንዳትችል የሚያደርግ አዳጋች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሊኖር ይችላል፤ ለአብነት የኢትዮጵያ ተራራማ ገጽታ ሴቶች እርዳታ ለማግኘት ሲሉ ለቀናት አንዲጓዙ የሚያስገድዳቸው ይሆናል።
  • ማኅበራዊ ተጽዕኖዎችም አንዲት ሴት ሕክምና እንዳታገኝ ሊያግዷት ይችላሉ ፤ ለምሳሌ ቤት ሆና ብትወልድ ይሻላል የሚል አስተሳሰብ ወይም ስለጤና ተቋማት ደኅንነት የተሳሳተ ግንዛቤ መኖር ይህንን ሊያስከትል ይችላል።

በኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ ማእከል ያለው የኛ ቡድን ሴቶች የሕክምና እንክብካቤ እንዳያገኙ የሚያርፉባቸውን ተጽዕኖዎች ለመከላከል እንሠራለን።

በወሊድ ወቅት ለሚፈጠር ፊስቱላ የሚሰጥ ሕክምና ምን ዓይነት ነው?


የሃምሊን አውታር በአሁኑ ወቅት በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላን ለማከም፤ በኢትዮጵያ ስድስት ፊስቱላ ላይ የሚያተኩሩ ሆስፒታሎች አሉት። ዋናው ሆስፒታል አዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን በመቀሌ፣ ይርጋአለም፣ ባሕርዳር፣ ሐረር እና መቱ የክልል ፊስቱላ ሆስፒታሎች አሉት።

ሃምሊን ለፊስቱላ በሚሰጠው ሕክምና በዓለም ዕውቅናን ያገኘ ሲሆን፤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ፊስቱላን ለማከም የሚደረግ የማስተካከያ ቀዶ ሕክምና ዙሪያ መልካም ተሞክሮን ለመቅሰም በሃምሊን ሆስፒታሎች ሥልጠና ይወስዳሉ። በዶ/ር ካትሪን ሃምሊን የተዘየደውን ይህንን ፈር ቀዳጅ የቀዶ ሕክምና ስልት ቀዳሚ የሆኑ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እውቅና ሰጥተውታል።

አብዛኛውን ጊዜ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ፤ በአንድ ዙር በሚደረግ ሕይወት ቀያሪ ቀዶ ሕክምና መስተካከል ይችላል። ነገር ግን በጣም ብዙ ዓመታት የተሰቃዩ አንዳንድ ሴቶች፤ ቁስላቸው ዘርፈ-ብዙ የሕክምና እንክብካቤ ሊፈልግ ይችላል።

በኢትዮጵያ ሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል ሴቶች ሕይወት ቀያሪ ሕክምና በነጻ ማግኘት ይችላሉ። ይህ እውን የሆነው ፊስቱላን ለማስወገድ ታጥቀው የተነሱ ሰዎች ማኅበረሰብ በዓለም ዙሪያ ስላለ ነው።

 በኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ ማእከል ስላለው የሕክምና ክትትል ይበልጥ ለመረዳት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ

በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላን እንዴት መከላከል ይቻላል? 


በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላን ለማጥፋት ተመራጩ መፍትሔ መጀመሪያውኑ እንዳይከሰት ማድረግ ነው።

ዶ/ር ሬጅ እና ካትሪን ሃምሊን በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ለመሥራት ያቀዱት ንጽሕናው እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወሊድ ሕክምና ለሁሉም ሴቶች ተደራሽ እንዲሆን አዋላጆችን ማሠልጠን ነው። እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ወደመጀመሪያ ውጥናቸው በመመለስ የሃምሊን አዋላጆች ኮሌጅን አቋቁመዋል።

የሃምሊን አዋላጆች ከኮሌጁ የሚመረቁት ለአራት ዓመት በመማር በሚያገኙት የአዋላጅነት የመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆን ከዛም ጊዜውን እና ደኅንነቱን የጠበቀ የእናቶች ጤና እንክብካቤ ለአካባቢው ሴቶች እንዲያቀቡ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እንዲሰማሩ ይደረጋል።

ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሴቶች እስካሁን ድረስ ሐኪም ወይም ነርስ አካባቢያቸው ሳይኖር ቤታቸው ውስጥ ይወልዳሉ። እጅግ አድጎ 115 ሚሊዮን የደረሰው የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር፤ ጥራት ያለውን የሕክምና እንክብካቤ ለማቅረብ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። የተቋማቱ በጊዜ ተደራሽ መሆን ፤ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላን ከመከላከል አንጻር ትልቅ ፋይዳ አለው።

ስለ ኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ ማእከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ጠለቅ ብሎ ለማንበብ ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ

የአሰገደች የሕይወት ታሪክ 


“በፊስቱላ የደረሰብኝን ጉዳት ለመጠገን ያገኘሁት የሕክምና ክትትል ሕይወቴን ቀይሮታል። አሁን የፈለግኩበት ቦታ እንደልቤ መንቀሳቀስ እና ያሰብኩን ሁሉ መሥራት እችላለሁ። ይህም ባለፉት 20 ዓመታት ከነበረኝ ሁኔታ ጋር ሲተያይ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው። እማዬ (ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን) እንዲሁም የሃምሊን ዶክተሮች ምስጋና ይግባቸው እና አሁን በጣም ተሽሎኛል…ሕይወቴን ቀይራችሁታል።” -ከአሰገደች አንደበት

አሰገደች ሕይወቱ ያለፈ ሕፃን ከወለደች እና የፊስቱላ ሕመም ካጋጠማት ጊዜ አንስቶ ሃምሊን በመምጣት ተስፋ እስከተዘራባት ድረስ ያላትን የሕይወት ገጠመኝ ስታስረዳ ለመስማት ይህንን ቪድዮ ይመልከቱ

https://youtu.be/heIFsIv0I5g