የቦርድአመራሮችእናዋናሥራአስፈጻሚ

ዶክተር ካትሪን ሃምሊን እና ዶክተር ሬጅ ሃምሊን 

መሥራቾች

ዶ/ር ካትሪን እና ዶ/ር ሬጅ ሃምሊን ከ63 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት  አዋላጅ ነርሶችን ያሠለጠኑ ፈር-ቀዳጅ የፅንስና ማሕፀን ሐኪሞች ነበሩ። ዶክተር ካትሪን አውስትራሊያዊ የነበሩ ሲሆን  ዶክተር ሬጅ ደግሞ ትውልዳቸው ኒው ዚላንድ ነበር።   ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ  ትኩረታቸው ሁሉ በማሕፀን ፊስቱላ ሕመምተኞች ችግር ላይ ሆነ። ሁለቱም አንድ ላይ በመሆን የማሕፀን ፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ዘዴዎችን ወደ ላቀ ደረጃ በማዘመን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሆስፒታሎችን በማደራጀት (ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያን በማቋቋም)፣ እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ገንቢ ግንኙነትን በመፍጠር ሕሙማንን ሲረዱ ቆይተዋል። እስካሁን ጊዜ ድረስ ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ቁጥራቸው ከ 70,000 በላይ የሆኑ ሴቶችን ረድቷል። ዶክተር ሬጅ እ.አ.አ. በ1993 (በ85 ዓመታቸው) እና ዶክተር ካትሪን እ.ኤ.አ. 2020 (በ96 ዓመታቸው) እስካረፉበት ጊዜ ድረስ በሃምሊን አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ እየኖሩ ታካሚዎችን ሲያክሙ ኖረዋል። ዶክተር ካትሪን ሁለት ጊዜ የሰላም ኖቤል ሽልማት ዕጩ ሆነዋል።  የኢትዮጵያዊ  ዜግነት በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ተሰጥቷቸዋል።

ዶ/ር መንግሥቱ አስናቀ

ሊቀመንበር

ዶ/ር መንግሥቱ ከጎንደር የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና ሳይንስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ኅብረተሰብ ጤና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በሥነ ተዋልዶ ጤና፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና አጠባበቅ፣ የሕፃናት ጤንነት፣ በማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት፣ በፕሮግራም ማኔጅመንት፣ በምርምርና ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ከ35 ዓመታት በላይ የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን በኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት (ከፍተኛ ባለሙያ) ናቸው። እ.ኤ.አ. ከ2006-2009 ድረስ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ማኅበር (ኢኅጤማ) ፕሬዝዳንት የነበሩ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ2012-2016 ድረስ ደግሞ  የዓለም ኅብረተሰብ ጤና ማኅበር (WFPHA) ምክትል ፕሬዝዳንትና ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል። ዶክተር መንግሥቱ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የፓዝፋይንደር ኢንተርናሽናል ከፍተኛ በኢትዮጵያ ተወካይ ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ፓዝፋይንደር በዓለም ላይ ካሉ ትልላቅ በእናቶች ጤና ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፋፊ ፕሮግራሞች አሉት። ዶክተር መንግሥቱ እ.ኤ.አ. ከ 2015 ጀምሮ  የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው ተሹመው የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ 2021 ጀምሮ ደግሞ ሊቀመንበር ሆነዋል።

ዶክተርይገረሙአበበአሰመረ

ዳይሬክተር

ዶ/ር ይገረሙ በሕክምና ሳይንስ ዲግሪ እና በኢንተርናል ሜዲስን (የውስጥ ደዌ ሕክምና) የድኅረ ምረቃ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጠቅላላ ሐኪምነት ሠርተዋል።  ዶ/ር ይገረሙ እ.ኤ.አ. በ 2006 በኢትዮጵያ የክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢንሺዬቲቭ ተወካይ ዳይሬክተር በመሆን ኤች አይ ቪ/ኤድስን እንዲሁም ሌሎች መቆጣጠር እና ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎችን በመዋጋት ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል። ከዚህ ኃላፊነታችውም ጡረታ የወጡት በቅርቡ ነው። እ.ኤ.አ. ከ 2015 ጀምሮ ደግሞ የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው ተሹመው በሥራ ላይ ይገኛሉ።

ዶክተርከበደወርቁ

ዳይሬክተር

ዶክተር ከበደ ወርቁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ሳይንስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ የፕሮግራም አስተዳደር እና ትግበራ ከፍተኛ ልምድ አላቸው። በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ናቸው። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሆነውም አገልግለዋል። በተጨማሪም የግሎባል ፈንድ አባል በመሆን የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የቲቢ እና የወባ ስርጭትን በመግታት ረገድ የበኩላቸውን የሥራ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በተጨማሪ የግሎባል ፈንድ አፍሪካ የምርጫ  ቢሮ ሰብሳቢ፣ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥነ-ምግብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሰብሳቢ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ብሔራዊ ፕሮግራም አፈጻጸሞች የበላይ ተቆጣጣሪ በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። ዶክተር ከበደ እ.ኤ.አ. ከ 2021 ጀምሮ  የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

ዶክተር ማሕሌት ይገረሙ ገብረማርያም

ዳይሬክተር

ዶ/ር ማሕሌት ይገረሙ ገብረማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፅንስና ማሕፀን ሕክምና አማካሪ ስፔሻሊስት ናቸው። ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ዲን እና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ። በሥነ ጾታና ሥነ ተዋልዶ ጤና የመብት ተሟጋች እና ተመራማሪ ናቸው። ዶክተር ማሕሌት እ.ኤ.አ. ከ 2021 ጀምሮ የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

አቶ ጀማል ካሳው

ዳይሬክተር

አቶ ጀማል ካሳው ኢንጅንደርሄልዝ በሚባለው ተቋም ውስጥ የኢትዮጵያ ተወካይ ሲሆኑ ከዚህ ድርጅት ጋር ለ16 ዓመታት አብረው ሠርተዋል። ከዚህ ቀደም የካናዳ ፊዚሺያንስ ፎር ኤይድ ኤንድ ሪሊፍ በተባለ ድርጅት ውስጥ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም አስተባባሪ እና የጤናና ሥነ-ምግብ አማካሪ በመሆን እንዲሁም የሥነ ተዋልዶ ጤና ማኅበራት ጥምረት የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን የማኅበረሰብ ጤና ላይ በሚሠሩ በርካታ ማኅበራት ውስጥ የሥርዓተ-ፆታ ፍትሐዊነት  እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና መብት ተሟጋች  በመሆንም ሠርተዋል።

አቶ ጀማል እ.ኤ.አ. ከ 2021 ጀምሮ የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

ወይዘሮ ታደለች ሽፈራው

ዳይሬክተር

ወ/ሮ ታደለች ሽፈራው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው እናት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ የዓለም አቀፍ (ኢንተርናሽናል) ባንኪንግ ዳይሬክተር ናቸው። እናት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማጠንከር ሕልም በነበራቸው 11 ባለራዕይ ሴቶች መሥራችነት የተቋቋመ ባንክ ነው። ወይዘሮ ታደለች በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የባንክ ኢንዱስትሪ እና አደጋ ቁጥጥር አስተዳደር (ሪስክ ማኔጅመንት) ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ወይዘሮ ታደለች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወይዘሮ ታደለች እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

ተስፋዬ ማሞ

ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አቶ ተስፋዬ በመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱ ናቸው።  ከእንግሊዝ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በትራንስፎርሜሽን ሊደርሺፕ እና ቼንጅ የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆንም ሠርተዋል። አቶ ተስፋዬ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሎጂስቲክስና ሰፕላይ ቼይን ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። አቶ ተስፋዬ ተስፋዬ የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የኦፕሬሽን እና የፕሮግራም አተገባበርን ከከፍተኛ የአመራሮች ቡድን ጋር በመሆን እየመሩት ይገኛሉ። እ.ኤ.አ. በ 2018 ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ 2019 ጀምሮ ደግሞ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ተሹመው በሥራ ላይ ይገኛሉ። አቶ ተስፋዬ ስለ ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ ብሩህ  ራዕይ አላቸው።