የሥልጠና አጋሮች

«ሃምሊን በጠቅላላ አነጋገር በሚሰጠው ክብካቤ ታካሚን ያማከለ  የልህቀት ማዕከል ነው። በሚገባ የተዋቀረ እና በየጊዜው እያደገ ያለ፣ ይበልጥ ማደግ የሚፈልግን ሰው ሁሉ የሚስብ ተቋም ነው።»

– ዶ/ር ቢኒያም ሲራክ የሃምሊን ይርጋለም ፊስቱላ ሆስፒታል  የሕክምና ዳይሬክተር እና የቀዶ ሕክምና ሐኪም

ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከሥልጠና አጋሮች ጋር በመሥራት የተሻለ የሕክምና አገልግሎት በሁሉም የሃምሊን ሆስፒታሎች እንዲሰጥ እና ከኢትዮጵያ ወሰን አልፎ እንዲጋራ ይሠራል። የሃምሊን ክሊኒካል ቡድን በሙያ ለማደግ እና ልዩ ችሎታዎችን ለማዳበር በሚያስችሉ ሥልጠና ዕድሎች የበቁ ናቸው። ዶ/ር ሬጅ እና ካትሪን ሃምሊን የማይናወጥ ወርቃማ እርካብን ገንብተዋል – ይህ ዛሬም ድረስ ለሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዋንኛ አጀንዳ ነው።

Iዓለምአቀፍየማሕፀንሕክምናእና የነፍሰጡር እናቶች ሕክምና ክትትል ፌደሬሽን (FIGO)


የፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ሥልጠና ተነሳሽነት 

ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን በማሠልጠን እና በማሕፀን ፊስቱላ ሕክምና የዓለም የልህቀት ማዕከል ሆኖ በመሥራት ረጅም ታሪክ እና ባህል አለው።

የሃምሊን አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል በ1974 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፈት የማሕፀን ፊስቱላ ያለባቸው ሴቶች ቀዶ ሕክምና ቴክኒክ እና አጠቃላይ ሕክምና ፋና ወጊ ከነበሩት ዶክተር ሬጅ እና ካትሪን ሃምሊን ለመማር የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ይመጡ ነበር። ይህ አሠራር ላለፉት ዐሥርት ዓመታት እያደገ የመጣ ሲሆን የሃምሊን የፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ለሌሎች የሕክምና ተቋማት የፊስቱላ ሕክምና ዘዴዎችን ለማሠልጠን ወደ ውጪ ሀገራትም ሄደዋል።

እ.ኤ.አ. በ2014 ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የማሕፀን ሕክምና እና የነፍሰጡር እናቶች ሕክምና ክትትል ፌደሬሽን (FIGO) ጋር በ‹ፊጎ (FIGO) ፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ሥልጠና ተነሣሽነት› ውስጥ በትብብርመሥራት ጀመረ። ይህ ተነሣሽነት ፊስቱላ የኅብረተሰብ ጤና ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ በቆየባቸው ዝቅተኛ ገቢ እና በቂ ሀብት በሌላቸው የዓለም ሀገራት የሠለጠኑ የፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ያለመ ነው። የቀዶ ሕክምና ሐኪሞችን ለማሠልጠን የማመልከቻው ሂደት በፊጎ በኩል ሲሆን የመጨረሻው ምርጫ የሚካሄደው በሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ሜዲካል ዳይሬክተር ነው።

የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች የፊስቱላ የቀዶ ሕክምና ክኅሎት እና የሃምሊን የሕክምና ሞዴል ዕውቀትን ለማግኘት በሃምሊን ይሠለጥናሉ። የሥልጠና መርሐ ግብሩ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን ለሁለት ሳምንት በአዲስ አበባ በሚገኘው የሃምሊን ዋና ሆስፒታል እና ለአራት ሳምንት በሃምሊን የክልል ሆስፒታሎች የሚካሄድ ነው።

ሥልጠናው ሁለት ደረጃዎች አሉት፤ መሠረታዊ የፊስቱላ ሕክምና እና ውስብስብ ለሆኑ ጉዳዮች የላቀ ቀዶ ሕክምና። ተሳታፊዎች ሥልጠናው ሲጠናቀቅ እና የፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ሐኪምነት የምስክር ወረቀት ሲያገኙ እነዚህን አዳዲስ ክኅሎቶች ወደ አካባቢያቸው ወስደው በፊጎ ዕውቅና ባለው የቀዶ ሕክምና ሐኪም ቀጣይነት ያለው የምክር አገልግሎት በመታገዝ ተግባር ላይ ያውላሉ።

ባለፈው ዓመት አምስት የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ከአፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ እና ኔፓል በሃምሊን አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል የሃምሊንን ምርጥ የፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ዘዴን ሥልጠና ወስደዋል። ሌሎች ስድስት አጋሮች በሚቀጥለው ዓመት ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን ድረስ ከዓለም ዙሪያ 30 የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች እና 11 ሌሎች (ነርሶች እና ፊዚዮቴራፒስቶች) የፊጎ ቀዶ ሕክምና ሥልጠና መርሐ ግብርን ተሳትፈው አጠናቀዋል። እነዚህ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች በማዳጋስካር፣ በጋና፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሌሎች የአፍሪካ፣ እስያ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ሴቶችን ለመርዳት የቀሰሙትን ትምህርት እየተጠቀሙ ነው።

እ.አ.አ ሴፕቴምበር 2022 የፊጎ ኤክስፐርት አማካሪ ቡድን ለፊስቱላ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች አዲስ የሥልጠና መመሪያን አሳትሟል። የፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ማሠልጠኛ መመሪያው ብዙ አዳዲስ ይዘቶችን፣ የቅርብ ጊዜ የቀዶ ሕክምና ቴክኒኮችን፣ አዲስ የቀዶ ሕክምና ምሳሌዎችን፣ የግድግዳ ቻርቶችን እና ሌሎችንም ይዟል። ይህ ማኑዋል ለፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ሥልጠና ፕሮግራሙ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የፊስቱላ ማኅበረሰብ መሪ የትምህርት ግብዓት ነው። የኤክስፐርት አማካሪ ቡድኑ በዶ/ር አንድሪው ብራውኒንግ የተመራ ሲሆን የሃምሊን አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር የሺነህ ደመረውም አንዱ የቡድኑ አባል ናቸው።

ፊስቱላ የሚያደርሰው አስከፊ ጉዳት በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ለዚህም ነው የማሕፀን ፊስቱላን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል ዓለም አቀፍ ትግል የሆነው። ሃምሊን ከኢትዮጵያ ድንበሮች ባሻገር ካሉ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ጋር በመሥራቱ ኩራት ይሰማዋል። በመተባበር፣ ዕውቀትን እና ክኅሎትን በማጋራት ይህንን መከላከል የሚቻል የወሊድ ጉዳት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ማጥፋቱ እንቃረባለን።

መቀሌ ዩኒቨርስቲ እና ዓለም አቀፍ የፊስቱላ ፈንድ  


የዩሮጋይናኮሎጂ ፌሎውሺፕ ፕሮግራም

እ.አ.አ. በ2015 ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የዩሮጋይናኮሎጂ ፌሎውሺፕ ፕሮግራም አዘጋጀ። ይህ የነዋሪነት ፕሮግራም በዩሮጋይናኮሎጂ ፣ በማሕፀን/የፊኛ/የዓይነምድር ከረጢት ሕክምና እና በመልሶ ሕክምና ቀዶ ሕክምና ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የሚሰጥ ንዑስ ልዩ ትምህርትን ያካትታል።

ፕሮግራሙ ለቀዶ ሕክምና ሐኪሞች የዓይነምድር ከረጢት እና የሽነት ቧንቧን መልሶ ለመቆጣጠር፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሽንት መውጫን አቅጣጫ ማስቀየርን፣ የኩላሊት ተግባርን መጠበቅ እና ሕይወትን ማሻሻልን የመሳሰሉ ውስብስብ የዩሮጋይናኮሎጂ ችግሮችን (ሁኔታዎችን) ለማከም የሚያስችል የላቀ እና ልዩ ችሎታዎችን ያጎናጽፋል።

ፕሮግራሙ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኩል ዕውቅና ተሰጥቶታል። ዓለም አቀፉ የፊስቱላ ፈንድም ለፕሮግራሙ የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እና የፕሮግራም ዳይሬክተሮችን እና የአካዳሚክ ሠራተኞችን በመመልመል ላይ እገዛ የሚያደርግ አጋር ድርጅት ነው።

ይህ የትብብር መርሐ ግብር የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ የሕክምና (ክሊኒካል) አገልግሎት ድርጅት እና በመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት የሕክምና ትምህርት ተቋም ትብብርን የሚያካትት፣ በጋራ ግብዓቶች እና የሙያ ተሞክሮዎች ባለሙያዎችን ለማሠልጠን እንዲሁም ቁጥራቸውን ለማብዛት ያለመ ትምህርታዊ መርሐ ግብር በማቋቋም የመጀመሪያው ነው።

ሥርዓተ ትምህርቱ ግልጽ የሆነ የመግቢያ መስፈርት እና የማጠናቀቂያ ቅድመ ሁኔታ አለው። በሞጁል ላይ የተመሠረተ ፕሮግራም ሲሆን እያንዳንዱ ሞጁል ሦስት የብቃት ደረጃዎች አሉት። ሠልጣኙ ሦስቱን የብቃት ደረጃዎች ማጠናቀቅ ያለበት ሲሆን በእያንዳንዱ ሞጁል ላይ በአንድ የፕሮግራሙ አካዳሚክ ባለሙያ አማካኝነት በችግር ላይ የተመሠረቱ ግምገማዎች ይደረጉበታል።

በተለምዶ የሥልጠና ክፍለ ጊዜዎች በሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ኔትወርክ የክልል የፊስቱላ ሆስፒታሎች ውስጥ ይከናወናሉ። ይህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ልዩ ሕክምና እንዲሰጥ፣ የዕውቀትና የክኅሎት ሽግግር እንዲኖር ዕድል ፈጥሯል።

እስካሁን በድምሩ ሰባት ባልደረቦች ፕሮግራሙን የተቀላቀሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 3ቱ አሁን በሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የፊት ለፊት የሥልጠና ክፍለ ጊዜ ባይቋረጥ ኖሮ ሁሉም ባልደረቦች አሁን ይመረቁ ነበር። መርሐ ግብሩ በጊዜያዊነት የቆመ ቢሆንም አዳዲስ የሰላም ስምምነቶቹን ተከትሎ በቅርቡ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

ፕሮግራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አራት የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ፌሎውሺፑን አጠናቀዋል። ሁለት ተጨማሪ የሃምሊን ክሊኒካል ቡድን አባላት ዶ/ር ለታ ገደፋ አራርሳ እና ዶ/ር ወንዱ በላይነህ ለቀጣይ ፕሮግራሞች ዕጩ ሆነው ተለይተዋል።

ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በመላው ኢትዮጵያ የዩሮጋይናኮሎጂ ፌሎውሺፕ ልማት እና ሥልጠና ላይ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ነው። ይህ ሥልጠና ሠልጣኞች ውስብስብ የሽንት ችግር ያለባቸውን፣ የፊስቱላ ሕክምናን፣ ፊስቱላ ያልሆኑትን ወይም የድኅህረ የማሕፀን/የፊኛ/የዓይነምድር ከረጢት ወደ ውጭ መውጣት ችግሮችን (ፒኦፒ) ምርጥ ዓለም አቀፍ ቴክኒኮችን በመጠቀም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲቆጣጠሩ ያስችላቸዋል።