የሃምሊንታሪክ

«ይህቦታለብዙዓመታትይኖራል፤ሁላችንምተባብረንፊስቱላንእሰክናጠፋድረስለብዙዓመታት… ኢትዮጵያውስጥያሉሴቶችሁሉጤናማወሊድእናጤናማልጅእስኪኖራቸውድረስ።» 

– ዶክተር ካትሪን ሃምሊን

ዶክተርካትሪን ሃምሊንእናዶክተርሬጅሃምሊን 


በታዋቂዎቹ በዜግነት አውስትራሊያዊ የሆኑት የቀዶ ሐኪሞች ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን እና ባለቤታቸው ዶ/ር ሬጅ ሃምሊን አማካኝነት ከስልሳ ዓመታት በፊት የተቋቋመው ሃምሊን ፊስቱላ-ኢትዮጵያ ሆስፒታል  እጅግ ዘግናኝ በሆነውና በወሊድ ጊዜ በሚያጋጥመው ኦብስትሪክ ፊስቱላ የተጠቁ ሴቶችን ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ተግቶ በመሥራት ላይ ይገኛል።

ኦብስትሪክ ፊስቱላ በወሊድ ወቅት በሚገጥም ከባድ እና ውስብስብ፣ በባለሙያ ያልታገዘ ምጥ ምክንያት የሚከሰት ውስጣዊ የአካል ጉዳት ነው። ኦብስትሪክ ፊስቱላ ያጋጠማቸው ሴቶች ሽንታቸውን የመቆጣጠር ችግር ስለሚኖርባቸው በዚህም በመሸማቀቅ  ጥልቅ ወደ ሆነ ሐዘን ውስጥ ይገባሉ። ስለ ኦብስትሪክ ፊስቱላ የበለጠ ለማወቅ ይህንን ይጫኑ

ዶክተር ሬጅ እና ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁትና በኋላም ለትዳር የበቁት በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ክራውን ስትሬት የሴቶች ሆስፒታል ውስጥ ሁለቱም የሕክምና ዶክተር እየሠሩ በነበሩበት ጊዜ ነው። በኦብስትሪሺያን ጋይናኮሎጂስትነት እንዲሠሩ እና የሚድዋይፈሪ (የአዋላጅነት ሙያ ሳይንስ) ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ እንዲያቋቁሙ በኢትዮጵያ መንግሥት  ጥሪ ሲቀርብላቸው በነበራቸው የአይበገሬነት መንፈስ ከባዱን ጥሪ በአዎንታ ተቀበሉት።

 እ.ኤ.አ. በ1959 ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ «በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፊስቱላ ሕሙማን ማየት ልብ ሰባሪ» እንደሆነ አንድ ጋይናኮሎጂስት ገለጸላቸው። መጥተው ሁኔታው ሲያዩትም እውነትም ልባቸው ተሰበረ።

በዚያን ወቅት ስለተሰማቸው ስሜት ካትሪን እንዲህ ብላ ነበር። «ገና መጀመሪያ ባገኘናት ታካሚ ልባችን ተሰበረ። በሐዘን ስሜት ተዋጥን። ቆንጅዬ ወጣት ሴት ነበረች… በሽንት የጨቀየ ልብስ ለብሳ  በሕሙማኑ ማቆያ ክፍላችን ውስጥ ከሌሎች ታካሚዎች ተነጥላ ብቻውን ተቀምጣ ነበር። ወዲያውኑ ከሌሎች ሕሙማን ይልቅ በቅድሚያ ሕክምና  ማግኘት እንዳለባት ተረዳን። እናም በወቅቱ ከነበሩት በርካታ የፊስቱላ ሕሙማን መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ሕክምናውን ለእሷ ሰጠን።»

እነዚህ ከአውስትራሊያ የመጡት ዕንቁ ዶክተሮች ኢትዮጵያን ጥለው ሄደው አያውቁም። ከናካቴው መኖሪያ ቤታቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች እና እናቶች የተሻለ የጤና ክብካቤ የሚያገኙበት ቦታ እንዲሆን በማድረግ ዶክተር ካትሪን እና ዶክተር ሬጅ ኑሯቸውን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ አደረጉ።

የጀመሩትን ሥራ ከምዕራፍ ሳያደርሱ ወደኋላ ማለት የማይወዱ እንደመሆናቸው ለኢትዮጵያውያን ሴቶች ጀርባችንን አንሰጥም በማለት ሳይታክቱ ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። አገሪቱ በወታደራዊ ውጥረት ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያት፣ በረሃብ ስትጠቃ፣ በዘግናኝ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ስታልፍ ሁሉ ሳያቋርጡ ለኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ ኋላ ሳይሉ ሙያዊ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ሥራቸውን ሀ ብለው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ የጀመሩት ዶክተር ካተሪን እና ዶክተር ሬጅ በወሊድ ወቅት የሚገጥሙ ችግሮችን ከማከም ጎን ለጎን በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን ፊስቱላ ለማከም ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን የቀዶ ሕክምና ቴክኒክ (ዘዴ) እንዲሻሻል አድርገዋል። ሥራቸውን በጀመሩባቸው በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ዶክተር ሬጅ እና ዶክተር ካትሪን በድምሩ ሦስት መቶ የፊስቱላ ሕሙማንን አክመዋል። በዚህም የሕክምናው ዜና በአገሪቱ በመሰራጨቱ  በርካታ ሕሙማን ወደ ሕክምና መስጫ ቦታቸው መጉረፍ ጀመሩ።

ይህንን ከፍተኛ የሆነ የኦብስትሪክ ፊስቱላ (በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም ፊስቱላ) ተጠቂዎች ለማስተናገድ የሚያስፈልገውን ወጪ ለማሰባሰብ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከተካሄደ በኋላ የአዲስ አበባ የፊስቱላ ሆስፒታል እ.ኤ.አ.  በ1974 ተመሠረተ።

ዶክተር ሬጅ ሃምሊን ሕይወታቸው እስካለፈበት እ.ኤ.አ.  1993 ድረስ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ አገልግለዋል። ከዶክተር ሬጅ ኅልፈት በኋላም ቢሆን ዶክተር ካትሪን ከኢትዮጵያ ርቀው መሄድ አልመረጡም። የሥራ ቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም የፊስቱላ ሕሙማን ሙሉ በሙሉ ሊድኑ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ ቀጠሉ። በአሁኑ ወቅት እየተሰጡ ያሉት የቀዶ ሕክምና (ቁስል) ማገገሚያ፣ የማማከር፣ የሕሙማን ማገገሚያ እና መልሶ ማቋቋሚያ ዘዴዎች… በአጭሩ ሁሉም የሃምሊን ሕክምና ሞዴሎች ለፊስቱላ ቅድመ ቀዶ ሕክምና እና ድኅረ ቀዶ ሕክምና ዘዴዎች በዓለም ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው ልዩ ዘዴዎች ለመሆን ችለዋል።

ዶክተር ካተሪን እና ቡድናቸው ተጨማሪ አምስት ሃምሊን ፊስቱላ ቅርንጫፍ ሆስፒታሎችን፣ የማገገሚያ እና የመልሶ ማቋቋሚያ ማዕከላትን እንዲሁም የፊስቱላ አደጋ ከመከሰቱ በፊት መቆጣጠር የሚያስችል የአዋላጅ ነርሶች የሥልጠና ኮሌጅን ለመክፈት ችለዋል። ኦብስትሪክ ፊስቱላን ከኢትዮጵያ የማጥፋት ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግም ዶክተር ካተሪን ሳያለሰልሱ ሥራቸውን መሥራታቸውን ቀጠሉ።

ዶክተር ካትሪን እ.ኤ.አ.  2020 እስካረፉበት ጊዜ ድረስ መኖሪያቸውን በአዲስ አበባ ሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ውስጥ አድርገው ቆይተዋል።

ሃምሊንፊስቱላኢትዮጵያበአሁኑወቅት


በአሁኑ ወቅት በሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ሥር የሚጠቃለሉ ተቋማት፦ ሃምሊን አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል፣ አምስት የክልል ፊስቱላ ሆስፒታሎች፣ የሃምሊን አዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ፣ ከ90 የሚበልጡ በሃምሊን የሚደገፉ የማዋለጃ ክሊኒኮች እና የሃምሊን ማገገሚያ እና መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል (ደስታ መንደር) ናቸው።

የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ አስተዳደር እና የተቋሙ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አብዛኞቹ ሃምሊን የሕክምና ሞዴሎችን በመጠቀም ለፊስቱላ ሕሙማን አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ በራሳቸው በዶክተር ካትሪን የሠለጠኑ ናቸው። የዶክተር ካትሪንን እና ዶክተር ሬጅን ራዕይ በማስቀጠልም ላይ ናቸው።

የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ቦርድ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን የሕክምና፣ የልማትና የንግድ ሥራ ባለሙያዎችን ያካተተ ሲሆን እነዚህ ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊያን እና መኖሪያቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉ ናቸው።
ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የኦብስትሪክ ፊስቱላን ከዓለም ላይ ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ውስጥ እንደ ዋቢ የሚቆጠር መሪ ተቋም ሲሆን የሴቶች ሰብአዊ ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ ጤናቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ሚናቸውን ጤናማ በሆነ መልኩ መወጣት እንዲችሉ የሚያደርግ ሁለንተናዊ የክምና እና ክብካቤ ክብካቤ መስጫ ተቋምን መገንባት ችሏል።
በዶ/ር ካትሪን ሃምሊን በመደገፍ የሃምሊን ሕክምና ቡድን ከ 70,000 በላይ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን አክሟል። የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዓላማ ፊስቱላን ከኢትዮጵያ ማጥፋት ነው። ማጥፋት የማይቻል ቢመስልም ይህንን ሕልም ዕውን ለማድርግ ታትረው የሚሠሩ ቁርጠኛ ደጋፊዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በማደጉ ምክንያት ሕልሙ እውነት ወደ የሚሆንበት ደረጃ እየተቃረበ ነው።

ሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የዶክተር ካትሪንን እና የዶክተር ሬጅን ከፊስቱላ የፀዳች ኢትዮጵያን የመፍጠር  ራዕይ ለማሳካት ቁርጠኛ አቋም አለው። በመሆኑም ፊስቱላ ከኢትዮጵያ እስካልጠፋ ድረስ ጉዞውን በጭራሽ አያቆምም።

>>ቪዲዮ ይቀጥላል «የዶክተር ካትሪን ጉዞ»