ጥናት

ሃምሊን በሚሰጠው ሁለንተናዊ የታካሚዎች እንክብካቤ የልህቀት ማዕከል ሆኗል። ተቋሙ በአግባቡ የተዋቀረ እና ሁሌም ዕድገት ያለበት በመሆኑ፤ ለወደፊቱ ማደግ የሚፈልጉ ማናቸውንም ሰዎች ትኩረት የሚስብ ነው

ዶ/ር ቢኒያም ሲራክ፤ የሕክምና ዳይሬክተር እና የቀዶ ሕክምና ባለሙያ፤ በሃምሊን ይርጋለም ፊስቱላ ሆስፒታል 

ዓለምአቀፍ ደረጃዎችን ማስቀመጥ


 ሃምሊን ፊስቱላ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ ወይም ሌሎች ጉዳቶች ለተከሰቱባቸው ሴቶች ሕክምና እና እንክብካቤ በመስጠትም ሆነ አስቀድሞ ይህ እንዳይፈጠር በመከላከል ረገድ ግንባር ቀደም በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ነው።

ለዐሥርት ዓመታት ዶ/ር ሬጅ እና ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን፤ በኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ በተሰማራባቸው መርሐግብሮች መልካም ተሞክሮዎች እና የጤና እንክብካቤ እንዲጎለብት የሚደረገውን ጥረት የመሩ ሲሆን፤ ወቅታዊ የሆኑ የምርመራ ጥናቶችን እና ፈጠራዎችን ለዓለምአቀፉ የሕክምና ማኅበረሰብ ለማቅረብ ሁሌም እንደተጉ ነበር።

ይህ እሳቤ በኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ ሕክምና እንዲሰርጽ ተደርጓል። የምርመራ ጥናቶች የድርጅታችን ዋንኛ ገጽታ ሲሆኑ በመረጃ ላይ የተመረኮዙ አዲስ አሠራሮች እና ዕድገቶችን ለማስገኘት መንገድ ይከፍታሉ።

በቅርቡ ቡድናችን የምርመራ ጥናት ክፍል ያዋቀረ ሲሆን፤ ይህንንም እንዲመሩ በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል የሚገኙትን አቶ ዮሃንስ ስጦታውን መልምሏል። መሪው በሃምሊን የምርመራ ጥናቶች እንዲካሔዱ እና የአሠራር ሥርዓት እንዲበጅላቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ባለፈው ዓመት፤ ይህ የምርመራ ጥናት ቡድን፤ የተለያዩ ጥናቶችን፣ የሕትመት መመሪያዎችን፤ እንዲሁም የምርመራ ጥናት ምክረሐሳብ እና የሪፖርት አጻጻፍ ማኑዋል ያዘጋጀ ሲሆን፤ ጥናት ሲያካሂዱ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ የሙያ ሥነምግባራት ለሠራተኞች ሥልጠና ተሰጥቷል። ሥልጠናው ተቋማዊ የግምገማ ቦርድ ለማቋቋም እንዲረዳ እንዲሁም የሚከተሉትን ጥናት የሚካሄድባቸው ጭብጦች ለማርቀቅ በማሰብ የተካሄደ ነው።

  • በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጉዳት እንክብካቤ
  • የእናቶች ጤና
  • የልጆች እና የጨቅላ ህጻናት ጤና
  • በጉርምስና ወቅት የሥነተዋልዶ ጤና
  • የሥነ ተዋልዶ ትምህርት

የምርመራ ጥናት ሐምሊን ፊስቱላ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዋንኛ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሆኖ ይቀጥላል። በአሁኑ ወቅት ስድስት የምርመራ ጥናት ምክረሐሳቦች ተጀምረው እየተሠሩ ይገኛሉ። ሌሎች ጅማሮ የሚጠብቁ ተጨማሪ የጥናት ምክረሃሳቦችም አሉ።

በቅርቡ የታተሙ ጥናታዊ ጽሑፎች


ከታች የሚታየው በቅርቡ በኢትዮጵያ የሃምሊን ፊስቱላ የሕክምና ሠራተኞች የተሳተፉባቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ዝርዝር ነው።