መጋቢት 10፣2012 ዓ.ም.
የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ መስራች ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን በ96 ዓመታቸው አረፉ
የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ መስራች የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ትላንት ሌሊት ረቡዕ መጋቢት 9 ቀን በ 96 ዓመታቸው አረፉ፡፡ ዶ/ር ካትሪን በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እና በሆስፒታሎች አስፈላጊውን ህክምና ሲከታተሉ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ1951 ዓ.ም ልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል በአሁኑ ጦር ሀይሎች አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዋላጅ ነርሶች ትምህርት ቤት ለማቋቋም ለሦስት ዓመት ኮንትራት አሁን በህይወት ከሌሉት ከባለቤታቸው ዶ/ር ሬጅናልድ ሐምሊንና ከ6 ዓመት ልጃቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዶ/ር ካትሪን የወሊድ ጉዳት የሆነውን ፊስቱላ ለማከምና ለመከላከል የሚያስችል ተቋም በመገባት ከ70,000 በላይ የአገራችን እናቶችና ወጣት ሴቶች እክምናውን በነፃ አግኝተው ወደ ቀደመው ህይወታቸው እንዲመለሱ አስችለዋል፡፡
በትውልድ አውስትራሊያዊ የሆኑት ዶ/ር ካትሪን በበጎ አድራጎት ስራቸው ከቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ የክብር ሽልማት፣ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያዊ ዜግነት የተበረከተላቸው ሲሆን በቅርቡ በድርጅታቸው 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከፍተኛ የኢትዮጰያ መንግስት የክብር ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችና ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን ሁለት ጊዜ ለኖቤል ሽልማት እጩ ሆነውም ቀርበዋል፡፡
በዶ/ር ካትሪን እና በባለቤታቸው ዶ/ር ሬጅናልድ ሐምሊን በ1966 ዓ. ም የተቋቋመው ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታልን ጨምሮ በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች አምስት የህክምና ማዕከላትን፣ የሐምሊን ሚድዋይፎች ማሰልጠኛ ኮሌጅን እንዲሁም የተጎጂዎች ማገገሚያና መልሶ ማቋቋምያ ማዕከል አካቶ የሚያስተዳድር ሲሆን በዓለማችንም ቀዳሚ ትኩረቱን ፊስቱላ ማከምና መከላከል ላይ አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ብቸኛ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡
በዶ/ር ካትሪን ዕልፈት ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸው፣ ለአጋሮቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናቱን እየተመኘን ስርዓተ-ቀብራቸውን በተመለከተ ዝርዝሩ ወደፊት እንደደረሰን የምናቀርብ ይሆናል፡፡
ዶ/ር ካትሪን የአንድ ልጅ እና የአራት ልጅ ልጆች እናት እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡